አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በቻይና (ሲፒሲ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የህብረተሰብ የሥራ ክፍል ም/ሚኒስትር ዛሆ ሺቶንግ (ዶ/ር) ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም÷ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች አጠቃላይ ሁኔታና የተገኙ ውጤቶች ላይ መክረዋል፡፡
የቻይና ኢንተርፕራይዞችና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው ሚናና ሚኒስቴሩ ቀጣይነት ባለው መልኩ የወሰዳቸው የፖሊሲና የአስተዳደር እርምጃዎች ላይ እንዲሁም በቀጣይ መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ÷ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ24 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ በመሳተፍ የአረጋውያን ቤት እድሳትና የደም ልገሳን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንደሰጡ ገልጸዋል።
የቻይና መንግስት እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉ የጤና ተቋማት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ያላቸውን ሚና እንዲያሳድጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዛሆ ሺቶንግ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ውይይት ካደረጉባቸው የቻይና ኩባንያዎች ጋር በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የተሻለ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መስማማታቸውን ተናግረዋል።