አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥሙ አምራቾችን እንደሚያበረታታ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
በላይነህ ክንዴ ግሩፕ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የገጣጠማቸውን በኤሌክትሪክ ሃይል የሚንቀሳቀሱ የከተማና መካከለኛ አውቶብሶች አስረክቧል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) እንዳሉት÷የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን ለማበረታታት እየተሰራ ነው፡፡
የቢኬጂ ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው÷ድርጅታቸው በአውቶሞቲቭ መገጣጠሚያና ምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ቢኬጂ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም በሀገር ደረጃ የራሱን አሻራ እያሠረፈ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቢኬጂ የተገጣጠሙትን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መጠቀም መጀመሩ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች በተሽከርካሪዎቹ ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
የተሽከርካሪዎቹ ባትሪ ለ15 ዓመታት እንደሚያገለግል ጠቁመው÷ኩባንያው ለባትሪ የ8 ዓመት እንዲሁም ለሞተር የ5 ዓመት ዋስትና እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።