የሀገር ውስጥ ዜና

በኢሬቻ በዓል መሳተፍ የሚፈልጉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከታች በተቀመጠው ሊንክ እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀረበ

By amele Demisew

September 24, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢሬቻ በዓል መሳተፍ የሚፈልጉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተዘጋጁ ልዩ ልዩ ሁነቶች ላይ ለመሳተፍ ከታች በተቀመጠው ሊንክ እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀረበ፡፡

ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከተያዙ ዝግጅቶች መካከል በመስከረም ወር የሚከበሩ ዋና ዋና በዓላት የሚገኙበት ሲሆን÷ ከበዓላቱ መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገልጿል፡፡

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበዓሉ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለማስተናገድም ክልሉ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀቱ ነው የተገለጸው፡፡

ለተጓዦች በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የትኬት ቅናሽ መደረጉ እንደተገለጸም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

ተጓዦች በቆይታቸው ልዩ ልዩ የቱሪዝም መስህቦችን የሚጎበኙበት፣ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት የሚያደርጉበትና በልዩ ልዩ የኢቨስትመንት ዘርፎች ላይ የሚሳተፉበት ዕድል መመቻቸቱም ተጠቅሷል፡፡

ስለሆነም በበዓሉ ላይ መታደምና ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በተመቻቹ ልዩ ልዩ ሁነቶች ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከታች የተቀመጠውን ሊንክ በመጠቀም እንዲመዘገቡ አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡