አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ጋር በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ በጋራ ለመስራት እና በፌደራል ፖሊስ ሥር የተቋቋመውን የሬድ ፎክስ ማዕከል በማቴሪያልና በስልጠና ለማጠናከር ያለመ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በውይይቱ ወቅት÷ ከእንግሊዝ የብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ ጋር እየተጠናከረ የመጣውን ትብብር አንስተዋል፡፡
በተለይ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ በጋራ ለመስራት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሥር የተቋቋመውን የሬድ ፎክስ ማዕከል በማቴሪያልና በስልጠና ለማጠናከር መክረዋል፡፡
ኮሚሽነር ደመላሽ ለተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በእንግሊዝ ሀገር እየተሰጠ ላለው የፊኖባንክስ የትምህርት ዕድል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም እድሎቹን በማስፋት እንዲሁም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተገነባ ያለውን የፎረንሲክ ማዕከል በማቴሪያል፣ በአቅም ግንባታ እና በልምድ ልውውጥ ለመደገፍ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው÷ ሀገራቸው በፀጥታው ዘርፍ ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይ ትብብሩን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በእንግሊዙ ብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ መካከል የሚፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡