አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቆሼ-ሚቶ-ወራቤ የመንገድ ፕሮጀክት አስፓልት የማንጠፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።
ስልጤ ዞንን ከማረቆ ልዩ ወረዳ ጋር የሚያገናኘው የቆሼ-ሚቶ-ወራቤ መንገድ ፕሮጀክት አፈጻጸም ያለበት ሁኔታ እየተጎበኘ ነው፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ 73 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን÷ በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በጀት በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ግንባታው እየተከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ሲጀመር በ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበር የገለጸው አስተዳደሩ÷ይሁን እንጂ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የፕሮጀክቱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ አለመቻሉን ጠቅሷል።
አሁን ላይ የ11 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር አስፋልት ንጣፍ ፣ የ68 በመቶ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት ፣ የ60 በመቶ ሰብቤዝ እንዲሁም የ16 በመቶ የቤዝ ኮርስ ሥራዎች መከናዎናቸው ተገልጿል።
የሁለት ድልድዮችን ግንባታ ጨምሮ የውኃ ማፋሰሻ ቱቦ እንዲሁም የአነስተኛና ከፍተኛ ከልቨርቶች ግንባታ ሥራ በፕሮጀክቱ መካተቱ ተመላክቷል።
ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሥራ አሁን ላይ 41 ኪሎ ሜትር ወይም 56 በመቶ የሚሆነው የተጠናቀቀ ሲሆን÷ የግንባታውን ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ ተናግሯል።
ስራ ተቋራጩ በተያዘው በጀት ዓመት 22 ኪሎሜትር የአስፋልት መንገድ በመስራት የፕሮጀክቱን አጠቃላይ አፈጻጸም 86 በመቶ ለማድረስ ማቀዱን አስታውቋል።
በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን በርበሬ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍና ሌሎች የጥራጥሬና የአዝርዕት ምርቶችን በፍጥነት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ እንደሚያስችልም ተገልጿል።
መሳፍንት እያዩ