አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የኮፐር መስመሮችን ወደ ፋይበር በመቀየር ዘመናዊ ባለገመድ ብሮድባንድ ኢንተርኔትና በዳታ ላይ የተመሰረተ የድምጽ አገልግሎት ለማቅረብ “ኮፐር ስዊች ኦፍ” የተሰኘ ኢኒሼቲቭ ማስጀመሩን አስታውቋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ የተጀመረውን ኢኒሼቲቭ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ከዚህ ቀደም የነበረው የኮፐር አገልግሎት በቴሌኮም ኢንዱስትሪው ከ150 ዓመታት በላይ ማገልገሉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም ለ130 ዓመታት ለደንበኞች የባለገመድ መደበኛ ስልክና ላለፉት 20 ዓመታት ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ ሲያገለግል ነበር ነው ያሉት፡፡
“ኮፐር ስዊች ኦፍ” ኢኒሼቲቭ የባለገመድ የቴሌኮም አገልግሎት ደንበኞችን ከነባሩ የኮፐር መስመር የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ወደሚያስችለው የፋይበር መስመር ያለምንም ክፍያ በነጻ ለመቀየር ያስችላል ተብሏል፡፡
ኢኒሼቲቩ በተያዘው በጀት ዓመት 100 ሺህ የኮፐር ደንበኞችን ወደ ፋይበር እንደሚያዛውርና በመጀመሪያው ምዕራፍም የ31 ሺህ ደንበኞችን መስመር ለመቀየር እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የኮፐር ኔትወርክ በፋይበር በመተካት የ10 ሺህ ደንበኞችን አገልግሎት ወደ ፋይበር ኔትወርክ ለመቀየር እቅድ እንደተያዘ ተመላክቷል፡፡
በአዲሱ የፋይበር ኔትወርክ መስመር ደንበኞች አሰራራቸውን ለማቀላጠፍና ለማዘመን የሚጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች የሚፈልጉትን ፍጥነት በላቀ ሁኔታ ማሟላት ከማስቻል ባለፈ አሁን የተዘረጋው የፋይበር ኔትወርክ ሳይቀየር የደንበኛው ፍላጎት ሲያድግ አቅሙን ከ1 ጂ ወደ 10 ጂ ብሎም ወደ 50 ጂ ለማሳደግ ያስችላል፡፡
እንዲሁም ለወሳኝ ተልዕኮ አገልግሎቶች እጅግ አስተማማኝ አገልግሎት ለማቅረብ እንደ ክላውድ እና ኤጅ ኮምፒውቲንግ፣ አይኦቲ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ኢንተርቴይንመንት፣ የዲጂታል ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ በርካታ ስማርት ሆም እና ሌሎችም የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡
የአዲስ አበባ ኮፐር ኔትወርክን በቀጣይ 3 ዓመታት፣ የክልል ዋና ዋና ከተሞችን ደግሞ በቀጣይ 5 ዓመታት እንዲሁም የዞን እና ወረዳ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ታቅዶ ትግበራ ተጀምሯል፡፡
በምንተስኖት ሙሉጌታ