Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ስራኤል በሂዝቦላህ ዒላማዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ስትፈፀም ታጣቂ ቡድኑም ምላሽ እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሊባኖስ በሚገኙ የሂዝቦላህ ኢላማዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈፀሟ ሲነገር ሂዝቦላህም በምላሹ በእስራኤል ግዛት የሮኬት ጥቃት እየፈፀመ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው÷ በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመው የአየር ጥቃት በርካታ የሂዝቦላህ ኢላማዎችን ማውደሙን አስታውቋል፡፡

በአየር ጥቃቱ ከ558 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ አካባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸውን የሊባኖስ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡

ሂዝቦላህ በበኩሉ÷ በእስራኤል ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ በፈፀመው የሮኬት ጥቃት ከእስራኤል መዲና 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የፈንጅ ፋብሪካ ማውደሙን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በሰነዘረው ሶስት ተከታታይ የሮኬት ጥቃት በሰሜናዊ እስራኤል የሚገኘውን መጊዶ አየር ማረፊያ ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል፡፡

ሂዝቦላህ ለሃማስ የሚያደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማስቀጠል ሮኬቶችን ወደ እስራኤል እያስወነጨፈ ነው ተብሏል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የተባባሰውን ጦርነት ተከትሎ ወደ ሊባኖስ መዲና ቤይሩት የሚደረጉ 30 ዓለም አቀፋዊ በረራዎች መቋረጣቸው ተነግሯል።

የኳታር፣ የቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አየር መንገዶች የውጥረቱ ሰለባ ናቸው መባሉን አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version