አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ አንጋፋውን የኦልድትራፎርድ ስታዲም በሁለት ቢሊየን ፓውንድ ወጪ ሊያድስ መሆኑን አስታወቀ፡፡
እድሳቱ ሲጠናቀቅ የስታዲየሙ ተመልካች የመያዝ አቅም ከ100 ሺህ በላይ እንደሚሆን ተገልጿል።
እንዲሁም ዕድሳቱ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
የኦልድትራፎርድ ስታዲየም እድሳት ፕሮጀክት የእንግሊዝን የቱሪዝም ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዩሮ ከፍ እንሚያደርገው ነው የተገለፀው፡፡
የእድሳት ፕሮጄክቱ ከ92 ሺህ በላይ የስራ እድሎችን ይፈጥራል የተባለ ሲሆን ከ17 ሺህ በላይ አዳዲስ ቤቶች ይገነቡበታል ተብሏል፡፡
በማንቼስተር ከተማ የሚገነባው አዲሱ የኦልድትራፎርድ ፓርክ ኮምፕሌክስ የእደሳት ፕሮጄክት የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ መዝናኛ፣ የንግድ እና የትምህርት ቤት ማዕከላት ይኖሩታል ተብሏል፡፡
ግንባታውን ለማጠናቀቅ ማንቼሰተር ዩናይትድ የማንቼስተር ከተማ ነዋሪዎች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ አለመጠየቁ የተገለፀ ሲሆን ግንባታው እስኪጠናቀቅ የትራንስፖርት ተርሚናሎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛውሩለት ጠይቋል፡፡
የቀድሞው የማንቼስተር ዩናይትድ ኮከብ ጋሪ ኔቭል እና የማንቼስተር ከተማ ከንቲባ አንዲ በርንሃም የፕሮጄክቱን ሂደት የሚከታተለው ግብረ ሀይል ሰብሳቢ ሆነው መመረጣቸውን ቶክ ስፖርት አስነብቧል፡፡