አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ49 ሺህ ሔክታር በላይ አዲስ መሬት በእንሰት ተክል መሸፈኑን የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ህብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የተለያየ ጠቀሜታ ያለውን የእንሰት ተክል ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ባንጉ በቀለ ተናግረዋል።
ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ንቅናቄ ከ49 ሺህ 450 ሔክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የእንሰት ችግኞች መትከል መቻሉን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በምርምር ከተለዩ 40 የእንሰት ዝርያዎች መካከል ከ80 በመቶ የሚልቁት ዝርያዎች በክልሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
ተክሉን ከበሽታ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ባለድርሻዎችን በማስተባበር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ የእንሰት ተክል ማልማት ባልተለመደባቸው አካባቢዎች ጭምር የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡