አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመሠላ በዓል የሀገር ሽማግሌዎች የምርቃት ሥርዓት የሚያደርጉበትና ሌሎችም ትእይንቶች የሚቀርቡበት ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ለመሠላ በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት÷ በዓሉ እንደ ዘመን መቁጠሪያ መሆኑን ጠቅሰው÷ የወራትና የዓመት መጀመሪያ ቀን ነው ማለት ይቻላል ብለዋል፡፡
ይህም በመላው በከምባታ፣ ጠንባሮ እና ዶንጋ ሕዝብ መካከል ልክ እንደ አሮጌ ዓመት መሸኛ እና አዲስ አመት መቀበያ ነው ተብሎ ይታመናል ሲሉ በመልእክታቸው ገልጸዋል፡፡
ልጅ ሲወለድ፣ መሳላ አንድ፣ መሳላ ሁለት፣ መሳላ ሦስት ተብሎ እንደሚጠራ በመግለጽ፤ ብዙውን ጊዜ ዓመትን ሲቆጥሩ 15 ዓመት የሆነውን ሰው አሥራ አምስት መሳላ ይባላልም ነው ያሉት፡፡
መሳላ ከጥንት አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና ህዝብ ሁሉ በጉጉት የሚጠባበቁትና ሲደርስ ደግሞ ቅድመ ዝግጅቱን በማሳመር ብዙ ባህላዊ ሥርዓቶችንና ክንውኖችን ይዞ የሚከበር ነዉም ብለዋል፡፡
በበዓሉ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ፀሎት የሚደረግበት፣ ለበዓሉ በሚሠዋው እንስሳ ላይ ሀገሩ ሠላም እንዲሆን፣ መልካም ፀሀይ እና ዝናብ በምድሪቱ ላይ እንዲወጣ፣ አዝመራው እንዲባረክ፣ ወቅቱ እንዲባረክ የሀገር ሽማግለሌዎች የምርቃት ሥርዓት የሚያደርጉበትና ሌሎችም ትእይንቶች የሚቀርቡበት ታላቅ ክብረ-በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከምባታ ብሔረሰብ በሁሉም ታላቅ ደጃፍ በሬ ይታረዳል፣ በዚያን ጊዜ ነው የአካባቢው ሽማግሌዎች ቀርበው ያንን ሰንጋ የሚመርቁት ያሉት ወ/ሮ ሸዊት÷ በዓሉ እንደ ዞን በአካባቢው በሚከበርበት ወቅት በዞኑ ለምርቃት የተመረጡ የሃገር ሽማግሌዎች ቆመው ይመርቃሉ፡፡
“ማሳሊ ባሪዱ” ወይም መሳላ የጥጋብ ቀን ተብሎ ስለሚቆጠር ሁሉም እኩል ጠግቦ እንዲያድር ይደረጋልም ማለታቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
አዲሱ ዘመን የሰላም፣ የጤና፣ የአብሮነት እንዲሁም ማህበራዊ ትስስር የሚጠነክርበት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡