አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንስሳት ጤና ኢኖቬሽን ሪፈረንስ ማዕከላት እና ክትባቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በጣሊያን ሮም ተጀምሯል፡፡
በኮንፈረንሱ ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፥ የእንስሳት ጤና እና ፈጠራ እንዲሁም የመከላከያ ክትባቶች ምርትና ስርጭት ለአፍሪካ ሀገራት ስላለው አስፈላጊነት አብራርተዋል፡፡
በዚህም የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ)፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና የተመድ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ድንበር ዘለል ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለማጥፋት ለሚያደርጉት ያልተቆጠበ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ግርማ(ዶ/ር) ስለአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የመስኖ የስንዴ ምርት እና ሌሎች በግብርና ዘርፍ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ የስኬት ታሪኮች ላይ አፅንዖት ሰጥተው ማብራሪያ መስጠታቸውን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።