የሀገር ውስጥ ዜና

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከ130 ሺህ በላይ ለሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጠረ

By ዮሐንስ ደርበው

September 23, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ130 ሺህ በላይ ለሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፈጠሩን የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኃይሉ የቴራ፤ 29 ፕሮጀክቶችን ያቀረቡ 24 ባለሃብቶች በፓርኩ ውስጥ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ መካከል በቡና ምርት ማቀነባበር የተሰማሩ 11 እንዲሁም በአቮካዶ ማቀነባበር ስራ ላይ የተሰማሩ ስምንት ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህም በተጨማሪ በአኩሪ አተር ዘይት ልማት፣ በወተት እና የማር ምርት ማቀነባበር፣ እንስሳት መኖ ልማትና የህጻናት አልሚ ምግብ ማቀነባበር የተሰማሩ ባለሃብቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከ130 ሺህ ከሚልቁ አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር እና ለ17 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ጋር የገጠር የሽግግር ማዕከላት ከዋናው ፓርክ ከ19 እስከ 80 ኪሎ ሜትር ዙሪያ የአርሶ አደሩ ግብዓቶች የሚሰባሰቡባቸው፣ የሚለዩባቸው ማዕከላት እንዳሉ መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በዚህም መሰረት አርሶ አደሮቹ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት ለኢንዱስትሪው ፓርኩ ግብአትነት በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።