ቢዝነስ

ከአዳማ-ጂቡቲ የቁም እንስሳት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ይፋ ሆነ

By ዮሐንስ ደርበው

September 23, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአዳማ ወደ ጂቡቲ የቁም እንስሳት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ይፋ መሆኑን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) አስታወቁ፡፡

ሥራአስፈጻሚው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ “ዛሬ ከአዳማ ወደ ጅቡቲ የመጀመሪያ የቁም እንስሳትን በባቡር ወደ ውጭ መላክ እንጀምራለን” ብለዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል ለገቢ ዕቃዎች ብቻ ያገለግሉ የነበሩ ክፍት ፉርጎዎችን በመጠቀም የቁም እንስሳቱን ወደ ውጭ መላክ እንደሚጀመር ነው የገለጹት፡፡

የቁም እንስሳቱን በባቡር ወደ ውጭ ማጓጓዙ በእንስሳት ላይ ያለውን የትራንስፖርት ጫና በመቀነስ የኤክስፖርት ስጋ ጥራትን እንደሚሳድግ አመላክተዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ለውጤታማ እና ዘላቂ ንግድ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ ኢትዮጵያ በድንበር ላይ የሚደረጉ የካፒታል ፍሰቶችን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡