አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላትን ለሚያስተባብሩ ከ310 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ስምሪት መሰጠቱ ተገለጸ።
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በዓሉን አስመልክቶ ውይይት ሲካሄድ፥ የስራ ስምሪት እንደተሰጠም ተገልጿል።
ስምሪቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም ፀጥታ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በመሆን ነው የሰጡት፡፡
በዓላቱ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ ወጣቶቹ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ የከተማው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር አሳስበዋል።
በዓላቱ የሚከበሩባቸው ቦታዎች እንዲሁም የአካባቢያቸውን ብሎም የከተማቸውን ሰላም ወጣቶች ነቅተው እንዲጠብቁ ገልጸው፥ በበዓላቱ እንዳይያዙ የተከለከሉ ነገሮችንና በኮሪደር ልማት የተሰሩ የልማት ስራዎችን እንዲቆጣጠሩ አሳስበዋል።
በከተማዋ ጥምር የሰላም እና የፀጥታ ግብረ ሀይል መቋቋሙንና ወደ ስራ መግባቱም ተነግሯል።
በዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ወጣቶች ከተቋቋመው ግብረ -ኃይል ጋር በመቀናጀት እንዲሰሩ መናገራቸውን ከከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡