አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 254 ሺህ ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የግብርና መምሪያ ሃላፊዎች እና ባለሞያዎች ጋር በመስኖና አጠቃላይ የግብርና ተግባራት ዙሪያ እየመከረ ነው፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ም/ሃላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በዘንድሮው ዓመት በክልሉ 11 ከመቶ የነበረውን የመስኖ ሽፍን ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡
በበጋ መስኖ ስንዴ ከ9 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እንደሚሰራ ጠቁመው÷ለዚህም 6 ሺህ 800 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ይሰራጫሉ ብለዋል፡፡
ሞዴል የመስኖ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና የተሟላ የግብርና ኤክስቴንሽኖችን ተግባራዊ በማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡
በዘንድሮው አጠቃላይ የመስኖ እንቅስቃሴ 342 ሺህ 480 ሔክታር መሬት ለማልማት እንደሚሰራና ከዚህም ከ47 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡
በእሸቱ ወ/ሚካኤል