አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የጸደቀው ስምምነት አፍሪካ ላይ እየደረሰ ያለው ኢ-ፍትሃዊነት እንዲታረም መንገድ እንደሚከፍት ጠቆሙ፡፡
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የ21ኛው ክፍለ-ዘመን ተግዳሮት ናቸው ያላቸውን በመቅረፍ በዓለም ላይ እየተከፋፈሉ ያሉትን ሀገራት አንድ ላይ ለማምጣት ያስችላል ያለውን እቅድ አጽድቋል።
ጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ግጭት፣ ኢ-እኩልነት እንዲሁም የድህነት መባባስ ዓለም አቀፍ ስጋት ሲል ከለያቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ 42 ገጽ ያለው የስምምነት ሰነድ “ፓክት ፎር ዘ ፊውቸር” በሚል ርዕስ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጠሩት የሁለት ቀን ጉባኤ መክፈቻ ላይ ጸድቋል።
ሰነዱ የወደፊት የዓለምን እጣ ፈንታ ያሻሽላል ተብሎ የታመነበትን ሲሆን፤ 193 የተመድ አባል ሀገራት መሪዎች የገቡትን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር ለዓለም ህዝብ ህይወት መለወጥ ምክንያት እንደሚሆን ታምኖበታል።
ሰነዱ ድህነትን ለማጥፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ፣ የጾታ እኩልነትን ለማስፈን፣ ሰላምን ለማስፈን፣ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ እና የባለብዙ ወገን ሥርዓትን ለማጠናከር “የዛሬንና የነገን እድሎች ለመጠቀም” በሚሉ ርዕሶች 56 ጉዳዮችን አካትቷል ተብሏል።
ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሰነዱ በርካታ ቁልፍ ድንጋጌዎች እንዲሁም ግሎባል ዲጂታል ኮምፓክት እና ስለወደፊት ትውልዶች እጣ ፈንታ ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች መካተታቸውን ገልጸዋል።
ስምምነቱ የዓለም ሀገራት መሪዎች 15 አባላት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲሻሻልና ከዚህ ጋር ተያይዞም በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ አለመኖርን ጨምሮ በአፍሪካ ላይ እየደረሰ ያለውን ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት እንዲስተካከል አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ እንደሚያግዝም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም የእስያ-ፓስፊክ ቀጣና እና የላቲን አሜሪካ በአግባቡ አለመወከልን በመለየት ችግሩን መቅረፍ እንደሚገባ በሰነዱ መካተቱን ተናግረዋል።
በዚህም የዓለም ችግሮችን ለመቅረፍ እርስ በርስ መነጋገር ብቻ ሳይሆን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መጠየቃቸውን አፍሪካ ኒውስ እና ኤፒ ዘግበዋል፡፡