Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ም/ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጠየቁ።

በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ የሆነውና ከ140 በላይ የሀገር መሪዎች የሚሳተፉበት የመጪው ጊዜ ጉባዔ ተከፍቷል።

በዚሁ ጉባዔ በአምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን እየተሣተፈ ይገኛል።

በጉባዔው ላይ ሚኒስትሩ ባሰሙት ንግግር የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጥ መልኩ እንዲከናወን ጠይቀዋል።

አምባሳደር ታዬ ምክር ቤቱን ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ የአፍሪካን የውክልና አድማስ ከሁሉም መመዘኛዎች አንጻር ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባው ጠይቀዋል።

ስምምነቱ ሁሉንም አገራት በእኩል አይን የሚመለከተው ጊዜ አይሽሬ የሆነው የተመድ መመሥረቻ ቻርተር ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ለማድረግ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በመጪው ጊዜ ጉባዔ ላይ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ሥርዓትን ሪፎርም ለማድረግ በትውልድ የአንድ ጊዜ ዕድል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ጉባዔ ሠነድ ከ143 አገራት በላይ ድጋፍ በማግኘት ፀድቋል።

አምባሳደር ታዬ ስምምነቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።

ሚኒስትሩ አገራት ድህነትን ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት በራሳቸው የፖሊሲ ማዕቀፍ ምርጫ አግባብ የተጠናከር ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ለጉዳዩ ቀዳሚ ትኩረት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው የፀደቁት ሠነዶች የድርድር ሂደት ላይ ተሳትፎ ስታደርግ መቆየቷን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

የሠነዱ መፅደቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ድህነት፣ ረሃብ፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ አደገኛ ግጭቶች፣ወረርሽኞች እና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች እያደጉ በሚገኙበት ወቅት፣የጋራ ምላሽ እና መፍትሄ ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

Exit mobile version