የሀገር ውስጥ ዜና

በጎንደር አብያተ መንግሥታት ውስጥ የሚገኘው ደብረ ብርሃን ሥላሴ አደጋ እንደተጋረጠበት ተገለጸ

By Shambel Mihret

September 22, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በተመዘገበው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ውስጥ የሚገኘው ደብረ ብርሃን ሥላሴ አደጋ የተጋረጠበት መሆኑ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንደገለጸው÷ የጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቅርስ ጥገና ካልተደረገለት ከፍተኛ የመፍረስ አደጋ ስለተጋረጠበት የባለድርሻ አካላትን ርብርብ ይፈልጋል።

የቢሮው የስራ ሃላፊዎች፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎችና የማኅበረሰብ ተወካዮች በዛሬው ዕለት የህንጻውን ውስጣዊና ውጫዊ የጉዳት ሁኔታ በተመለከቱበት ወቅት፤ ቅርሱ የጥናትና ዲዛይን ሥራ ተሠርቶ ዘላቂ ጥገና ካልተደረገለት ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን ባለሙዎች ገለጻ አድርገዋል።

ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው ጎንደር ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከስነ ህንጻ አሠራሩ ጀምሮ በውስጡ በያዛቸው ከ300 ዓመታት በላይ ባስቆጠሩ ሥዕላቱ የሚታወቅና ከጎንደር አብያተ መንግሥታት ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት የሚጎበኘው የዓለም ቅርስ መሆኑም ተነግሯል።

ታሪክን ለትውልድ ለማስቀጠልና ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ልዩ ቦታውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል፣ የቅርስ ተቆርቋሪዎችና ኢትዮጵያውያን ርብርብ እንዲያደጉም ተጠይቋል።

በደሳለኝ ቢራራ