Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጥምር የፀጥታ ሃይሉ አስታውቋል፡፡

በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በርካታ የተለያዩ ኩነቶች ያለምንም የፀጥታ ችግር መከበራቸውን ያስታወሰው ጥምር የፀጥታ ሃይሉ፤ ኩነቶቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ የፀጥታ ሃይሉ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ ሰርቷልም ተብሏል፡፡

የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓልም በድምቀት ተከብሮ እንዲያልፍ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

የፀጥታ አካላት ለሚያከናውኑት ተግባር በተዘጋጀው ዕቅድ ውይይት በተደረገበት ወቅት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ÷ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ከሐይማኖቱ አባቶችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጥምር የጸጥታ ሀይሉ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዳይጠናቀቅ ፍላጎት ያላቸው አካላትን ሴራ ለማክሸፍ ልዩ ልዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው÷ የፀጥታ ሃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ በመግባት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መፈፀም የሚችልበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ በዓሉ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ጥምር የፀጥታ ሃይሉን በመደገፍ በኩል ህብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ÷ በዓሉ ወደሚከበርበት ስፍራ ከበዓሉ አከባበር ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ነገሮች ይዞ መምጣት ክልክል መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ለፀጥታ ሃይሎች ስራ ተባባሪ እንዲሆን አስገንዝበዋል።

Exit mobile version