ቢዝነስ

ኢንዱስትሪው “ዋይ ቲ ኦ” እና “ኒው ሆላንድ” ትራክተሮችን መገጣጠም እንደሚጀምር አስታወቀ

By ዮሐንስ ደርበው

September 21, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በ2017 የበጀት ዓመት “ዋይ ቲ ኦ” እና “ኒው ሆላንድ” የተሰኙ ዘመናዊ ትራክተሮችን መገጣጠም እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

ኢንዱስትሪው የሀገሪቱ ግብርና እንዲዘምን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ኢንዱስትሪው በያዝነው የበጀት ዓመት “ዋይ ቲ ኦ” እና “ኒው ሆላንድ” የተሰኙ ዘመናዊ ትራክተሮችን መገጣጠም እንደሚጀምር ማረጋገጣቸውን የግሩፑ መረጃ አመላክቷል፡፡

የሀገሪቱ የግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ እንዲያድግ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች ሚና ከፍተኛ ነው፤ ይህን ለማሳካት የተቋቋመው የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪም ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራት የበለጸጉት ቴክኖሎጂ ላይ በመሥራታቸው መሆኑን አስገንዝበው÷ የምርምር ሥራዎች ላይ በማተኮር ኢትዮጵያዊ ምርቶችን ማምረት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል በሚል መሪ ቃል እየሠራን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡