Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የ “ማሽቃሮ/የቤነ ሻዴዬ ባሮ” በዓልን ስናከብር በመረዳዳት ይሁን- ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የካፊቾ ብሔር የዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ/የቤነ ሻዴዬ ባሮ ” በዓልን ስናከብር በመረዳዳት ሊሆን ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ ለ”ማሽቃሮ/የቤነ ሻዴዬ ባሮ” በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በዓሉ በካፊቾ ብሔር ዘንድ በድምቀት የሚከበር እና ከአሮጌው ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንና መሰል የጥንት አባቶች ጠብቀው ያቆዩትን ትውፊቶችና ባህሎች በማልማት ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኃላፊነት ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዓሉ ሲከበርም ያለው ለሌለው በማካፈል፣ አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን በመጠየቅ እና የማሽቀሮን ባህላዊና ትውፊታዊ ዕሴቶችን ሙሉ በሙሉ በማንፀባረቅ መሆን አለበት ብለዋል ።

በዓሉ የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት እንዲሆንም ተመኝተዋል።

Exit mobile version