Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

“ዮዮ ጊፋታ” ሳይሸራረፍ ለትውልድ እንዲሸጋገር ሕዝቡ በቅንጅት እንዲሠራ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝባዊ መሰረት ያለው“ዮዮ ጊፋታ” በዓል ተጠናክሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ሕዝቡ በቅንጅት እንዲሠራ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስገነዘበ፡፡

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ለ2017ዓ.ም የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ “ጊፋታ” ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ሲከበር መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በዓሉ የወላይታ ሕዝብ አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት የሚቀበልበት የብሔሩ ዘመን መለወጫ መሆኑንም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ፍቅርና አብሮነት የሚገለጽበት፣ መተሳሰብና መረዳዳት የሚተገበርበትና መጭው ዓመት የሰላምና የደስታ እንዲሆን ወደ ፈጣሪ የሚጸለይበት በዓል መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

በተጨማሪም የታመሙ የሚጠየቁበት፣ የታሰሩ የሚጎበኙበት የተቸገሩ የሚረዱበት የመረዳዳትና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ሕዝባዊ መሰረት ያለው በዓል ይበልጥ ተጠናክሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይሸራረፍ እንዲተላለፍም ለማድረግም ሕዝቡ በቅንጅት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ለሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት÷ ያሆዴ ጥላቻና ቂም በቀል ተወግዶ ሰላም የሚወርድበት የአዲስ ዓመት መግቢያ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ያላት መሆኗን በመገንዘብ÷ በየብሔሩ የሚገኙ ባህሎችን በመጠበቅ ለሕዝቦች አንድነትና ለማኅበራዊ ትስስር መጠቀም አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

እነዚህ ቱባ ባህሎች ሳይሸራረፉ ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በጋራ እንረባረብ  ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version