የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የመኸር ወቅት ልማትን ስኬታማ የሚያደርግ የእንክብካቤና የጥበቃ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

By Meseret Awoke

September 21, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2016/2017 የመኸር ወቅት ልማትን ስኬታማ የሚያደርግ የእንክብካቤና የጥበቃ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻው እንደገለጹት÷ በክልሉ 2016/2017 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች ተሸፍኖ እየለማ ነው።

የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግም ከ7 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ቀርቦ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ለመኸር ሰብል ልማት ስራው ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

ይህም በቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።

በምርት ዘመኑ ለሰብል ልማት ስራው አመቺ የሆነ የዝናብ ስርጭት መኖር፣ የጎላ የተባይ ክስተት አለመኖር እየለማ ያለው ሰብል አሁን ላይ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በመኸር ወቅቱ በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ከሚገኘው መሬት 169 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው ፥ የሰብሉ ቁመናም ይህንኑ በሚያሳካ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የምርት ዕቅዱን በተሟላ መንገድ ለማሳካት የአረም መከላከል፣ የኩትኳቶ፣ የተባይ አሰሳና ጥበቃ ስራው በተቀናጀ አግባብ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ይህም የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ለማረጋገጥ እየለማ ከሚገኘው ሰብል ውስጥ 100 ሚሊየን ኩንታል ለምግብ ፍጆታ ቀሪው ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ እንደሚውልም አቶ አጀበ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።