አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለወላይታ፣ ጋሞ እና ጎፋ ዞን ሕዝቦች የዘመን መለወጫ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ ፥ ዮ ማስቃላ በጋሞ ዞን በድምቀት የሚከበር የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን ፤ በርካታ ባህላዊ እሴቶችን በውስጡ የያዘ ነው።
የጋሞ ” ዮ ማስቃላ” ፣ የጊዲቾ “ባላ ካዳቤ” እና የዛይሴ ” ቡዶ ከሶ ” የዘመን መለወጫ በዓላት በጋሞ ዞን ከሚከበሩ ቱባ ባህላዊ ክብረ በዓላት መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ ተገልጿል ።
ዮ ማስቃላ ለጋሞዎች የአንድነት፣ የመቻቻል፣ የእርቅና የሰላም ማብሰሪያ የሆነ ጥላቻ ተወግዶ ፍቅር የሚነግስበት በደስታ በፌሽታ የሚከበር ትልቅ በዓል እንደሆነ ይታወቃል።
በጎፋ ዞን የሚገኙ ነባር ብሔረሰቦች የጎፋ እና የኦይዳ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነው የ”ጎፋ ጋዜ ማስቃላ” እና የ”ኦይዳ ዮኦ ማስቃላ በክልሉ በድምቀት የሚከበር በዓል እንደሆነ ተጠቅሷል።
በዓሉ ያለፈውን ዓመት ሀዘን የምንቋጭበት አዲሱን ዓመት በደስታ የምንቀበልበት በመሆኑ በጌዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት ናዳ መላው የሀገራችንና የዓለምን ህዝቦችን ካስደነገጠውና በርካታ ዜጎችን ካጣንበት መሪር ሀዘን የምንወጣበት በዓል በመሆኑ ለመላው የጎፋ ማህበረሰብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ዮ ጊፋታ የወላይታ ህዝብ አሮጌውን ዘመን ሸኝቶ አዲሱን የሚቀበልበትና ተራርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማድ ተገናኝተው በፍቅር የሚያከብሩት በዓል ነው።
ጊፋታ መደጋገፍና መተሳሰብ ጎልቶ የሚታይበት የተቀያየሙና የተቃቃሩ የሚታረቁበት፣ ቂምና ቁርሾ ያላቸው በጊፋታ ይቅር ተባብለው አዲሱን ዓመት በንፁህ ልቦናና በፍጹም ደስታ ይቀበሉታል።
በዚህም እንኳን ለጊፋታ በዓል አደረሳችሁ ዘመኑ የስኬት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡