Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ተመድ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የሚደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት የመንግስታቱ ድርጅት (ተመድ) ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የሚደርገውን ድጋፍ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ።

25ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን “የሰላም ባህልን ማሳደግ” በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ሚኒስቴር፣ የተመድ፣ የሰብዓዊ መብትና የሰላም ግንባታ ተቋማት እንዲሁም የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከብሯል።

በኢትዮጵያ የተመድ የልማት ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ሳሙአል ዶ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በታሪክና ብዝኅነት የበለጸገችና ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለመፍጠር የምትተጋ ሀገር ናት።

በዚህም የህዝቦቿን አንድነትና የጋራ ብልጽግናን ለማስቀጠል የሰነቀችውን ራዕይ ፍትሕ፣ እኩልነትና ተስፋን የተጎናጸፈ የሰላም ባህል ለማዳበር የምታደርገውን ጥረት ተመድ ይደግፋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደትና የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ዘላቂ የሰላም ግንባታን በመፍጠር ዜጎች በመተማመን እንዲኖሩ ለማድረግ የማይተካ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

የሰለጠነ ውይይት ማድረግ ልዩነትን በመግባባት ለመቀየር ያስችላል ያሉት ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር)፤ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትም የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላምና በውይይት በመፍታት መተማመን ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ልማቷን ለማስቀጠል በምታደርገው ጥረት ተመድ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተለይም ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የሴቶችንና ወጣቶችን ሚና ማሳደግ የሚያስችሉ አጀንዳዎችን ላይ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ስራ አስፈፃሚ አወቀ አጥናፉ(ዶ/ር)፤ ሰላም በምንም አይነት ዋጋ ሊተመን የማይችል ከራስ የሚመነጭ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሁሉም ዜጋ የተሟላ ሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ቀጣይነት ላለው የሰላም ግንባታ ሂደት በባለቤትነት መንፈስ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

የተመድ ኤጀንሲዎችም ለሴቶችና ለወጣቶች፤ በበጎ አድራጎትና ልዩ ልዩ የስልጠና ስራዎች ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

Exit mobile version