የሀገር ውስጥ ዜና

ግምቱ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ንብረት በመስረቅ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

By Shambel Mihret

September 20, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ግምቱ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ንብረት በመስረቅ የተጠረጠሩ እና ተቀባዮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 10፡30 ላይ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በግንባታ ላይ በሚገኘው አዳምስ ህንፃ ላይ የተዘረጉ የኤሌትሪክ ገመዶችን ለመስረቅ ሁለት ተጠርጣሪዎች አጥር ዘለው ሲገቡ በወቅቱ በወንጀል መከላከል ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ተይዘው ሲፈተሹ የኬብል መቁረጫና ሁለት ቦርሳ እንደተገኘባቸው ተጠቅሷል፡፡

የተፈፀመውን ወንጀል መነሻ በማድረግ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ የማካሄድ ሥራ መስራቱን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላታል፡፡

በምርመራ ማስፋት ሥራ ግለሰቦቹ በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 በፀጋ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኝ አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት የሰረቁትን ንብረት እንደሚያስረክቡ በመረጋገጡ በህግ አግባብ በተደረገ ብርበራ 50 ጥቅል የኤሌትሪክ ገመዶች፣ 5 ጥቅል የኤል ኢ ዲ ኬብል፣ ልዩ ልዩ አይነት ሌሎች ኬብሎች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከአዳምስ ህንፃ የተሰረቁ የኤሌትሪክ ገመዶች መገኘቱንም ፖሊስ አስታውቋል።

ከዚህ የወንጀል ድርጊት ጋር በተገናኘ የስርቆት ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩና የተሰረቀ እቃ የሚገዙ ሁለት ተቀባዮች ተይዘው ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡