የሀገር ውስጥ ዜና

ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የዝሆን ጥርስ አምጥተው ሊሸጡ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት ቀረቡ

By ዮሐንስ ደርበው

September 20, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዝሆን ጥርስ ከትግራይ ክልል ሽረ ከተማ ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ሊሸጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉት ሐይማኖት አባዲ ግርማይ እና መገርሳ ቡልቻ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻና የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ ተመልክቷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በሕገ ወጥ መንገድ የዝሆን ጥርሶችን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ገነት ሆቴል አካባቢ መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም ቀን 6 ሠዓት ላይ ሊሸጡ ሲሉ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የክትትል ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሶ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የጥርጣሬ መነሻውን አብራርቷል።

በዚህ መነሻ የዝሆን ጥርሶችን በዱር እንስሳት ባለስልጣን ባለሙያዎች እንዲረጋገጥ በማድረግ የምርመራ ማጣሪያ ሥራ መጀመሩን የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ÷ የምስክር ቃል ለመቀበልና ግብረ አበር ለመያዝ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

1ኛ ተጠርጣሪ በቦሌ አራብሳ እንደምትኖር እና የባህል አልባሳት እንደምትሸጥ ጠቅሳ÷ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ግንኙነት የለኝም በማለት ተከራክራለች፡፡

2ኛ ተጠርጣሪ በበኩሉ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪና የሞባይል ጥገና የሚሠራ ባለሙያ መሆኑን ገልጾ÷ ከተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም ሲል ተከራክሯል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ÷ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ለፖሊስ መስጠት ተገቢ መሆኑን በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄን ለጊዜው በማለፍ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ውስጥ የ10 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

የምርመራ ማጣሪያ ውጤት ለመጠባበቅም ለመስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ