የሀገር ውስጥ ዜና

ኢራን የሀገሪቱን ብሄራዊ መዝሙር አላከበረም ያለችውን የታሊባን ዲፕሎማት ለማብራሪያ ጠራች

By Shambel Mihret

September 20, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገሪቱን ብሄራዊ መዝሙር አላከበረም ያለውን የታሊባን ዲፕሎማት ለማብራሪያ መጥራቱ ተሰምቷል፡፡

የታሊባን የሃጅና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ም/ሚኒስትር አዚዙርማን መንሱር ለማብራሪያ የተጠሩት በቴህራን በተዘጋጀ ጉባዔ ላይ የኢራን ብሄራዊ መዝሙር ሲዘመር ከመቀመጫቸው ባለመነሳታቸው ነው ተብሏል፡፡

የዲፕሎማቱ ድርጊት የሀገሪቱን ብሄራዊ ክብር የነካ ነው በሚል የኢራንን ባለስልጣናት ክፉኛ ማስቆጣቱ ነው የተነገረው፡፡

በቴህራን የታሊባን ተወካይ ፋዛል ሞሃመድ ሃቃኒ÷ ድርጊቱ የግለሰቡን የግል ሥነ-ምግባር እንጂ የታሊባንን አቋም አይወክልም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

ዲፕሎማቱ ብሔራዊ መዝሙሩ ሲዘመር ተነስተው ክብር ባለመስጠታቸው ይቅርታ መጠየቃቸውንም አሙ ቲቪ ዘግቧል፡፡

በአንጻሩ በአፍጋኒስታን የኢራን አምባሳደር ሀሰን ካዝሚ ቆሚ÷ድርጊቱ የሼሪዓን ደንብ ያላከበረና አስነዋሪ ነው ሲሉ ይቅርታውን አጣጥለዋል፡፡

ድርጊቱ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊያሻክር እንደሚችልም ተመላክቷል፡፡