የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ1 ሺህ 100 ሄክታር ላይ ምርጥ ዘር እየለማ መሆኑ ተገለጸ

By Shambel Mihret

September 20, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ1 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ የተለያየ ሰብል ምርጥ ዘር እየለማ መሆኑንም የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የተያዘውን የመኸር እርሻ ጨምሮ በበልግና በመስኖ ልማት በ2016/17 ምርት ዘመን ከ131 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ እንደገለጹት÷ በተያዘው ምርት ዘመንም ይህን ለማሳካት በሦስቱም ወቅቶች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል።

የክልሉን የግብርና ልማት ለማሳደግ የግብዓት አጠቃቀም እንዲሁም ኩታ ገጠም የግብርና ልማት ሥራን ማጠናከርና ማስፋት ቅድሚያ እንደተሰጠውም አቶ ሃይለማርያም አንስተዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅት ብቻ 769 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱንም በመግለጽ ከእዚህ ውስጥ በ1 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ የበቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ማሽላ፣ ስንዴ እና ጤፍ ምርጥ ዘር እየለማ ነውም ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡