የሀገር ውስጥ ዜና

አንዲት እናት በአንድ ጊዜ 4 ሕፃናት ተገላገሉ

By Shambel Mihret

September 19, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓዊ አጠቃላይ ሆስፒታል የ42 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እናት በአንድ ጊዜ አራት ሕፃናትን ተገላገሉ።

ወይዘሮ አደባባይ የሺነህ ነዋሪነታቸው በአዊ ብሔረሰብ ዞን ጃዊ ወረዳ አሊኩራንድ ቀበሌ ሲሆን÷ በዛሬው እለት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ በሚገኘው ፓዊ አጠቃላይ ሆስፒታል ነው ሶስት ወንድና አንድ ሴት የተገላገሉት።

ጨቅላ ህጻናቱ ጊዜያቸው ሳይደርስ በሰባት ወር የተወለዱ በመሆኑ በህፃናት ፅኑ ህሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በሆስፒታሉ መንታ መውለድና አልፎ አልፎም አንዲት እናት እስከ ሶስት ሕፃናትን በአንድ ጊዜ መገላገል የተለመደ ቢሆንም በአንድ ጊዜ አራት ሕፃናትን ሲወለዱ ግን የአሁኑ የመጀመሪያ መሆኑን ሚድዋይፈሪ ሞገስ ጌታቸው ተናግረዋል።

ወላጅ እናት የአሁኑን ጨምሮ ለስድስተኛ ጊዜ የወለዱ ሲሆን÷ በአሁኑ ሰዓት በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የህክምና ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ አደባባይ በሰላም እንዲገላገሉ ለረዷቸው የሕክምና ባለሙያዎችና የፓዊ ወረዳ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ምስጋና ማቅረባቸውን የፓዊ ወረዳ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡