Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የምክከር ሂደቱን በአካታችነትና አሳታፊነት ማጎልበት የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል – መስፍን አርአያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምክከር ሂደቱን በአካታችነትና አሳታፊነት ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካል ሀላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

የአገው ለፍትሕ እና ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነፃነት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመስራት የመግባባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም ከኮሚሽኑ ጋር ከመስራት ራሳቸውን አግልለው የነበሩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ፓርቲዎቹ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት ከኮሚሽኑ ጋር በመስራት የምክክሩን ሂደቱን ለማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

በምክክር ሂደቱ መሳተፋቸው አስፈላጊ መሆኑን በማመን በሂደቱ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመሳተፍ እንደተዘጋጁም አረጋግጠዋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት÷ የምክከር ሂደቱን በአካታችነት እና አሳታፊነት ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካል ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በምክክር ሂደቱ ከመሳተፍ ታቅበው የነበሩት የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ፣ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር እና የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከኮሚሽኑ ጋር ስምምነት ፈጥረው በምክክሩ እየተሳተፉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሌሎች ያልተሳተፉ የፖለቲካ ድርጅቶችም የሂደቱ አካል እንዲሆኑ ጥሪ መቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version