አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብርና ሚኒስቴር አርብቶ አደሩ የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የእንስሳት ኢንሹራንስ ግዢ እንዲያከናውን ጥሪ አቀረበ፡፡
የእንስሳት ኢንሹራንሱ ሽያጭ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ነሀሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡
በዓመት ሁለት ጊዜ በሚከናወነው የኢንሹራንስ ሽያጭ በዚህ ዓመት ለ80 ሺህ አርብቶ አደሮች ኢንሹራንስን ለመሸጥ አቅድ መያዙ ተገልጿል።
በመሆኑም በመጀመሪያው ዙር ለ35 ሺህ አርብቶ አደሮች ኢንሹራንስ ለመሸጥ መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡
አርብቶ አደሩ በድርቅ ምክንያት እንስሳቱን እንዳያጣ አስቀድሞ አካባቢዎቹ በሳተላይት ከተለዩ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ውሀ፣ ሳር እና መድኃኒትን ለእንስሳት ለመግዛት እንዲቻል ኢንሹራንሱ ይከፈላል ተብሏል።
ኢንሹራንሱ ተግባራዊ የሚደረገው ዝናብ ሲመጣ አረንጓዴ ሆነው በተቃራኒው ደግሞ ዝናብ ሲጠፋ ደረቅ የሚሆኑት አካባቢዎች ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ኢንሹራንሱ የሚተገበረው በዓለም ባንክ ድጋፍ እና በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት በተቋቋመው የአርብቶ አደሮች የአደጋ ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነትና በአጋር ድርጅቶች እገዛ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በዚህ አመት በሚሸጠው ኢንሹራንስ 30 በመቶውን አርብቶ አደሩ ሲከፍል 70 በመቶው ደግሞ በፕሮጀክቱ ይሸፍናል ተብሏል።
በፍቅርተ ከበደ እና መሳፍንት እያዩ