የሀገር ውስጥ ዜና

በየነ ጴጥሮስ(ፕ/ር) የሰሩት ስራ የሚያኮራ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Meseret Awoke

September 19, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በህይወት ሳሉ የሰሩት ስራ የሚያኮራ በመሆኑ ትውልድ ከእርሳቸው ህይወት ሊማር ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የአስከሬን ሽኝት በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

በሽኝት መርሐ ግብሩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በህይወት ዘመናቸው የሰሩት ስራ የሚያኮራ በመሆኑ ትውልድ ከእርሳቸው ህይወት ሊማር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሽኝት መርሐ-ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የስራ አጋሮችና ወዳጆቻቸው በተገኙበት እየተከናወነ ነው።

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከቆዩ አንጋፋ ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር)÷ የተፎካካሪ ፓርቲው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡

የተለያዩ ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘውን የመድረክ ፓርቲንም በሊቀ-መንበርነት የመሩ ሲሆን÷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት እንዲሁም የትምህርት ምክትል ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው የሚታወስ ነው፡፡

በፍሬሕይዎት ሰፊው