አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መርህን መሰረት ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማራመድ እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ላይ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ÷ ኢትዮጵያ ቀጣናውን የትርምስ አውድማ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና በመሰረተ ልማት የተሳሰረ ጉርብትና እንዲኖር ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ማንም ለሚያነሳው ሀሳብ ምላሽና እንካስላንትያ እንደማትገጥም በመግለጽ፤ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የትርምስ አውድማ ለማድረግ የሚስተዋለው እንቅስቃሴ ግን ሊቆም ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መርህ ችግሮችን በሰከነ ውይይት መፈታት አለበት የሚል ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት÷ ነገር ግን ጉዳዩን መስመር እንዲስት ለማድረግ የሚሰነዘሩ ሀሳቦች ተገቢ አይደሉም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከመስከረም 14 እስከ 20 ቀን 2017 በመሪዎች ደረጃ በሚከናወነው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በንቃት ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጎባኤ ለ79 ዓመታት በንቃት መሳተፏን ጠቅሰው÷ በቀጣዩ ጉባኤም የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ትሳተፋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በንቃት እንደምትሳተፍም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ከአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ ሰራዊት አዋጭ ሀገራት ጋር የጎንዮሽ ውይይት እንደምታደርግም ተገልጿል፡፡