Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢጋድ ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት የቱሪዝም ሚኒስትሮች የኢጋድ ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታን ይፋ አድርገዋል።

ፍኖተ ካርታው በምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ማሳደግ የሚያስችል አቅምን ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በመርሐግብሩ የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት የቱሪዝም ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።

ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)÷በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ የሆነ የቱሪዝም እድገት እንዲመዘገብ የኢጋድ ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

የቀጣናው የጋራ የቱሪዝም ተጠቃሚነት በትብብር እንዲያድግ ኢጋድ ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በ10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ ሀገራቱ ያላቸውን የተፈጥሮ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ከማውጣትና ከመጠቀም ባለፈ የሕዝቦች ባህል እንዲጠበቅና እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።

ለፍኖተካርታው መሳካት መንግስታት፣ የግሉ ሴክተር፣ ሲቪል ተቋማትና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው÷ የኢጋድ ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ በቀጣናው ያለውን የቱሪዝም ሃብት ችግር ለመቅረፍና በጋራ ተጠቃሚ ለመሆን ያግዛል ብለዋል።

የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመገንባትና በማስፋፋት እንዲሁም ለዘርፉ የሚያስፈልገውን የመሠረተ ልማት በማሟላት ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በዓለም ላይ በቱሪዝም ከታደሉ ድንቅ ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ አንድሪው ሞልት ናቸው፡፡

የኢጋድ ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተካርታ በፈረንጆቹ ከ2024 እስከ 2034 ድረስ እንደሚቆይ ተጠቁሟል፡፡

በዓለምሰገድ አሳዬ

Exit mobile version