የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የተገነቡ መስኅቦች ለቀጣናው ሀገራት በጥሩ ማሳያነት እንደሚጠቀሱ ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

September 18, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የተገነቡ የቱሪዝም መስኅብ ስፍራዎች ለቀጣናው ሀገራት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ሀገራት የቱሪዝም ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ እንጦጦ ፓርክ እና በሳይንስ ሙዚዬም ጉብኝት አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት የደቡብ ሱዳን የዱር እንስሳት ጥበቃ እና ቱሪዝም ሚኒስትር ራዚክ ዛካሪያ ሀሰን÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና መንግስታቸው በአጭር ጊዜ የሚያኮራ የመስህብ ልማት ስራ ሰርተዋል ብለዋል።

የጎበኟቸው የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችም የአፍሪካዊያን መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ ከነበሯት ቀደምት ቅርሶች ባሻገር ለዘርፉ ልማት አቅም የሚሆኑ አስደናቂ የልማት ስራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የተከናወኑ የቱሪዝምና የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችም ከተማዋን ውብ ገጽታ ያላበሱና ለቀጣናው ሀገራት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የዑጋንዳ የቱሪዝም የዱር እንስሳትና ጥንታዊ ቅርሶች ሚኒስትር ዴዔታ ባሂንዱካ ማርቲን ሙጋራ በበኩላቸው÷ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ኢትዮጵያዊያን ለነፃነታቸው የከፈሉትን ውድ ዋጋ የሚያስታውስ ድንቅ የታሪክ ማስታወሻና ቋሚ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ ማድረጓም ከዘርፉ ያላትን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያግዝና እድገቷንም የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

በኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ዓለማየሁ ጌታቸው÷ ጉብኝቱ የቀጣውን ሀገራት የቱሪዝም ልማት ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የቀጣናው ሀገራትም በቱሪዝም መስክ ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንዲያሳልጡ ለማስቻል ልምድና ተሞክሮ የተለዋወጡበት አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል።