የሀገር ውስጥ ዜና

ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የአ/አ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ

By ዮሐንስ ደርበው

September 18, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብር መጠንን በመቀነስ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የአዲስ አበባ ፖሊስ መርማሪ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻንና የተጠርጣሪ ጠበቃ መከራከሪያ ነጥቦችን ተመልክቷል።

ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታዩት ተጠርጣሪዎች የአ/አ ገቢዎች ቢሮ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት የታክስ ኦዲት ቡድን አስተባባሪ ሃብታሙ ግዲሳ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ስምረት ገ/እግዚአብሔር፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ዮሴፍ ባቡ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር አቤኔዘር ቶሎሳ፣ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ለሚ ሲሌ እና ገንዘብ ተቀባይ ባለሙያ ወ/ሮ መቅደስ አረጋዊ ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን የስራ ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው ከግብር ከፋይ ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከግብር ከፋይ ድርጅቶች “ግብር እንቀንስላችኋለን” በማለት በመደራደር ከ100 ሚሊየን ብር የግብር መጠንን ወደ 13 ሚሊየን ብር ዝቅ በማድረግ ግብርን በመቀነስ ከተለያዩ ድርጅቶች በተለያዩ መጠኖች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ ተቀብለዋል በማለት መርማሪ ፖሊስ የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በባንክ ሂሳባቸው የጉቦ ገንዘብ ገቢ የተደረገላቸው ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡን በማመላከት ተጨማሪ ግብረ አበር ለመያዝና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ማስረጃዎች አሰባስቦ ለመቅረብ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ በበኩሏ ደንበኞቿ በመርማሪ ፖሊስ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት “አልፈጸሙም ” በማለት በመከራከር የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቃለች።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ በማለት በጠበቃቸው የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ በመጠየቅ ተከራክሯል።

የፖሊስ የጥርጣሬ መነሻን እና ግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የምርመራ መዝገቡ ጅምር በመሆኑ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ለፖሊስ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የተጠርጣሪ የዋስትና ጥያቄን በማለፍ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ