የሀገር ውስጥ ዜና

የጽዱ ኢትዮጵያና አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሮች ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ወሳኝ መሆናቸው ተመለከተ

By amele Demisew

September 18, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጽዱ ኢትዮጵያና አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሮች ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር መሰረት የሚጥሉ ንቅናቄዎች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

ምቹ መንደርና ጽዱ ሀገር መፍጠር ዜጎች ተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እንዲጠበቁ እንደሚያደርግም ነው ሚኒስትሯ ያስገነዘቡት፡፡

በዚህም ተቋማቸው በእግረኛ መንገዶች ደረጃቸውን የጠበቁ የመጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መጸዳጃ ቤቶችን ከመቀየር ባለፈ የአኗኗር እና የአመጋገብ ዘይቤን ጭምር መቀየር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጽዱ ኢትዮጵያና አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሮች ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር መሰረት የሚጥሉ ንቅናቄዎች ስለሆኑ ጤና ሚኒስቴር በዚህ ረገድ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ለዚህም ከከተማ አሥተዳደሮች፣ ከዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና አጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡