Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርን መጠን ለድርጅቶች በመቀነስ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከፍተኛ ኦዲተሮችን፣ ገንዘብ ተቀባዮች እና ቡድን መሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ከግብር ከፋይ ድርጅቶች “ግብር እንቀንስላችኀለን “በማለት በመደራደር በጥቅም በመመሳጠር ከ100 ሚሊየን ብር የግብር መጠንን ወደ 13 ሚሊየን ብር ዝቅ በማድረግ ግብርን በመቀነስ ከተለያዩ ድርጅቶች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል የተጠረጠሩ የቢሮው ግብር ከፋይ ጽ/ቤት ከፍተኛ ኦዲተር፣ ገንዘብ ተቀባይ እና ቡድን መሪ እንዲሁም ደላሎችን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የስነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሚሽን እና ፍትህ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በተደረገ ኦፕሬሽን ከመስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል።
በአሁን ወቅት ተጠርጣሪዎቹ ላይ የምርመራ ማጣሪያ ስራ የተጀመረ ሲሆን ከሰዓት በኋላ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ይሆናል።
በታሪክ አዱኛ
Exit mobile version