የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ካሉ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ ጋዜጠኞች ጋር ውይይት ተካሄደ

By amele Demisew

September 18, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ክፍል በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ካሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የውጭ ጋዜጠኞች ጋር ውይይት አካሄደ።

የውይይቱ ዓላማ ሚዛናዊ እና ተጨባጭ የዘገባ ሽፋንን ማሳደግ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ፈጣን የለውጥ እና ልማት ሂደት ውስጥ እንደመገኘቷ ጋዜጠኞች የጠራ መረጃ ብሎም ዝርዝር ግንዛቤ ማግኘታቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።

መሰል ግንኙነቶች በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ የዜና ሽፋኖች የኢትዮጵያን እድገት የሚያንፀባርቁ፣ ለፈተናዎቿ እውቅና የሚሰጡ ብሎም መንግሥት ለአካታች እድገት እና ዘላቂ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ እንዲሆኑ ያግዛሉ ተብሏል።

አፍሪካ በዓለም አቀፋዊው ሚዲያ የምትሸፈንበት ትርክት በአብላጫው በበሽታ፣ በድህነት፣ በግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት መልኮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጾ፤ ይህ ምስልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለአፍሪካ ያለውን አመለካከት እና የፖሊሲ ውሳኔ እየቀየሰ መቀጠሉ ተጠቅሷል።

በመሆኑም የዛሬው ውይይት ሚዛናዊ እና ምሉዕ እይታ ያለው የዘገባ ሥራን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥቶ የተነጋገረ ለወደፊቱም ለዚህ አይነቱ አዘጋገብ መጠናከር መንገዶችን የተመለከተ ነበር ተብሏል።