Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያና ፈረንሳይን የሁለትዮሽ ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ የሁለትዮሽ  ግንኙነት በይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ምክክር ተደረገ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ፈረንሳይ የወዳጅነት ቡድን ከፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የወዳጅነት ቡድን ጋር ተወያይቷል፡፡

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ፈረንሳይ የወዳጅነት ቡድን ዋና ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚሁ ወቅት÷ የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ብሔራዊ ጥቅም መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደምትገኝ ገልጸው÷ ማሻሻያው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ወዳጅ ሀገራት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው ዓለም የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አሸባሪዎችን ከመዋጋት አኳያ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይና ሌሎች አጋር ሀገራት ጎን ትቆማለች ማታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበርና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ግንኙነት በመፍጠር አካባቢያዊ ሰላም እንዲረጋገጥ በትጋት እየሠራች መሆኗንም ነው ያስረዱት፡፡

በፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የወዳጅነት ቡድን መሪ ሴናተር ሁግ ሳሪ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለፈረንሳይ ታሪካዊ አጋር መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው አፍሪካ ሽብርተኞችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሠራም ነው የገለጹት፡፡

የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም አስተዳደራዊ ዕድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠል በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ለመደገፍ ፈረንሳይ ትብብር ታደርጋለች ማለታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version