የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉልህ ሚና የምትጫወት ሀገር ነች- የፈረንሳይ ም/ቤት የአፍሪካ ቀንድ ወዳጅነት ቡድን

By ዮሐንስ ደርበው

September 17, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ጉልህ ሚና የምትጫወት ሀገር መሆኗን የፈረንሳይ ምክር ቤት የአፍሪካ ቀንድ ወዳጅነት ቡድን ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በሴናተር ሂዩግ ሶሪ ፕሬዚዳንትነት የተመራውን የፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ ወዳጅነት ቡድን አባላትን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ግንኙነት ታሪካዊ እና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፈረንሳይ በኢትዮጵያ በልማት ትብብር፣ በባህል፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የምታደርገውን ተሳትፎም አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና መልከዓ-ምድራዊ እና ስትራቴጂካዊ አቀማመጡ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው በመሆኑ የበርካታ አካላትን ትኩረት የሳበ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና እያደገ ከመጣው ምጣኔ ሀብቷ አኳያ ባሕር በር ወሳኝ በመሆኑ በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት እያደረገችው ያለውን ጥረትም አብራርተዋል።

በሶማሊያ ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አትሚስ) በኋላ የሚኖረው የኃይል ስምሪት በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው ማስረዳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የፓርላማ አባላቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ጉልህ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን በመግለጽ÷ የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ መጠናከር እንደሚገባው አንስተዋል።