የሀገር ውስጥ ዜና

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ደህንነት ጋር ተያይዞ ክስ የቀረበባቸው ግለሰቦች የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

By Meseret Awoke

September 17, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ደህንነት ጋር ተያይዞ ክስ የቀረበባቸው ሥድስት ግለሰቦች ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ዮሐንስ ዳንኤልን (ጆን ዳንኤል) ጨምሮ በሥድስት ግለሰቦች ላይ ወደ መቐለ ለመጓዝ በአየር ፀባይ ምክንያት በረራው ከተሰረዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አውሮፕላን አንወርድም በማለት ያለአግባብ መያዝ ወንጀል፣ የመንግስት ሰራተኛ የስራ ግዴታውን እንዳይፈጽም መቃወምና አለመታዘዝ የሚል ክስ መቅረቡ ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም በ1ኛ ተከሳሽ ደግሞ የአየር መንገዱን መልካም ስም የሚያጎድፍ በተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒውተር ስርዓት አማካኝነት ማሰራጨት የሚል የወንጀል ክስ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዐቃቤ ሕግ ማቅረቡ ይታወሳል።

በዚህ መልኩ የቀረበባቸው ክስ ለተከሳሾች ከደረሰ በኋላ በተከሳሾች ጠበቆች በኩል ደንበኞቻቸው የተከሰሱበት ድንጋጌ በመርህ ደረጃ ዋስትና ሊያስከለክል አይችልም በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፥ የወ/መ/ስ/ህግ ቁጥር 67/ለ ጠቅሶ በልዩ ሁኔታ ዋስትና ሊያስከለክል ስለሚችል በሰበር ሰሚ ችሎት ትርጉም የተሰጠባቸው ማለትም ከወንጀሉ ከባድነትና ከክሱ ተደራራቢነት፣ ከጉዳዩ ባህሪና ከከባቢያዊ ሁኔታዎች አንጻር ዋስትና ሊያስከለክሉ የሚችሉበትን ትርጉም የተሰጠባቸው የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥሮችን ጠቅሶ የዋስትና መብታቸው እንዲታለፍ ጠይቆ ነበር።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ወንጀል ችሎት የግራ ቀኝ የዋስትና ክርክሩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት ብይን ሰጥቶበታል።

በዚህም ተከሳሾቹ ከቀረበባቸው ተደራራቢ ክስ አንጻር ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም በማለት የጠየቁት የዋስትና ጥያቄን ውድቅ ተደርጎ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ታዟል።

ክሱን ለመመልከትም ለጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረጉት ተከሳሾች ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

በታሪክ አዱኛ