አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ሀገር የህክምና ቡድን አባላት ከተለያዩ የህክምና ተቋማት የተውጣጡ የጨቅላ ህፃናት ስፔሻሊስቶች በአለርት ሆስፒታል በጨቅላ ህፃናት ህክምና ላይ ስልጠና እየሰጡ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ስልጠናው በኢትዮጵያ ያለውን የጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ የአለርት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ፀጋዬ ገብረአናንያ ተናግረዋል።
የህክምና መሳሪያዎች እጥረትና ብቁ የሰው ሀይል እጥረት ለጨቅላ ህፃናት ሞት መጨመር ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ስልጠናው አቅምን የሚያሳድግ ተጨማሪ እውቀት የሚገኝበት መሆኑን ገልጸዋል።
የህክምና ቡድኑ ከስልጠናው በተጨማሪ ለተለያዩ ሆስፒታሎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማደረጉን በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ቶሜር ባር ላቪ ተናግረዋል።
መሰል ድጋፎችና የትብብር ስራዎች የእስራኤል እና ኢትዮጵያ ግንኙነትን የበለጠ እንደሚያጠነክርም ጠቁመዋል።
በቅድስት አባተ