የሀገር ውስጥ ዜና

ለሽግግር ፍትሕ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

By Meseret Awoke

September 17, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሽግግር ፍትሕ የተሟላ ትግበራና ፍትህን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።

በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና በማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰጠ ነው::

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር)፥ የሽግግር ፍትሕ የተሟላ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሽግግር ፍትሕ የተበደሉ ዜጎች የሚካሱባት፣ ሰላም፣ መረጋጋት፣ እርቅና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባትም መሰረት የሚያኖር መሆኑንም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ችግሮችን በእርቅ፣ በካሳ፣ በይቅርታና የተጠያቂነት መርህ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፥ ለዚህም የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የፖሊሲ ዝግጅት ስራው ተጠናቆ የፖሊሲ መተግበሪያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በዚህ የአሰራር ሂደት በደሎችን በማከም ሠላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የህዝብ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዝብ ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን የማስተማርና የማስገንዘብ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ለሽግግር ፍትሕ የተሟላ ትግበራና ፍትህን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና አላቸውም ብለዋል።

በዚህ የአሰራር ሂደት በደልና ቁርሾዎችን በመፍታት የተሻለ ነገን የሚፈጥር ማህበረሰብ መገንባት እንደሚገባ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።