የሀገር ውስጥ ዜና

በተለያዩ ክልሎች የ2017 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ተጀመረ

By amele Demisew

September 17, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ክልሎች የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፖክ ካዊች በ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራትና ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ይሠራል ብለዋል።

የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት እንዳይኖርና ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ ድጋፍ ይደረጋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል።

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2017 የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ማቴዎስ ማልደዮ÷ በክልሉ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል ምዝገባ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በቅድመ መደበኛ ከ403 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለመቀበል ምዝገባው ተከናውኖ ወደ መደበኛ ሥራ ተገብቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቡልቶሳ ኢርኮ (ዶ/ር) የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑም በ37 ሺህ 941 ትምህር ቤቶች ከ12 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ መግለጻቸውን ሪፖርተራችን ተስፋዬ እጅጉ ዘግቧል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን መማር ማስተማር ሂደት ዛሬ መጀመሩን የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ እየሩስ መንግሥቱ፤ በትምህርት ዘመኑ በክልሉ 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን በመመዝግብ ለማስተማር ታቅዷል ብለዋል።

ዘንድሮ 92 ሺህ ተማሪዎችን ለማስተማር በመዘገበው የሐረሪ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት መሰጠት መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ዘከሪያ አብዱልአዚዝ ማስታወቃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን ዛሬ በይፋ መጀመሩን የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር)፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት እና የተቋማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሙሐመድ ኡስማን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑ ከ300 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

በድሬዳዋ አሥተዳደር የ2017 ዓ.ም የመማር ማስተማሩን ስራ የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቡበከር አዶሽ በተገኙበት የተጀመረ ሲሆን÷ በዚሁ ወቅት በክረምት ወራት የትምህርት ቤቶች ደረጃዎች እና ምቹነት የማረጋገጥ ስራዎች በህዝብ ንቅናቄ መሠራቱን ኃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማነት አስፈላጊውን ግብዓት የማሟላት እና የመምህራንን አቅም የማሳደግ ስራም ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡