ቴክ

በበይነ-መረብ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮችና መከላከያ መንገዶች

By Meseret Awoke

September 17, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በይነ-መረብ (ኢንተርኔት) የዕለት ተዕለት የህይወት ዘይቤን ከቀየሩት የዓለም ክስተቶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡

በዚህም በኦንላይን ግብይቶች ይፈጸማሉ፤ የገንዘብ ልውውጦች እንዲሁም የተለያዩ ጉዳዮችን ለመፈጸም በአካል መገኝት ሳያስፈልግ የሚፈጸሙ ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በይነ-መረብ በሚጠቀሙበት ወቅት ብዙ ዓይነት ማጭበርበሮች መከሰታቸው አይቀሬ ሲሆን ፥ የማንነት ስርቆትና በኦንላይን ግብይቶች ላይ የሚከሰቱ ማጭበርበሮች ገንዘብዎን ለመመንተፍ የተቀየሱ ናቸዉ።

እራስዎን ከኦንላይን አጭበርባሪዎች እንቅስቃሴ ለመጠበቅ የሚከተሉትን መንገዶች ተግባራዊ ያድርጉ፡-

• የሙሉ አገልግሎት ኢንተርኔት መጠቀም፡- የሚጠቀሙት ኢንተርኔት ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶች እንዲኖሩት ማድረግ እንደ አብነት አዳዲስ የሚፈጠሩ ማልዌሮችንና ቫይረስን የሚከላከል መሆኑን ማወቅ፤

• ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም፡- ተገማች ያልሆኑና በቁጥር በምልክት እንዲሁም በቃላት የተሰባጠሩ የይለፍ-ቃሎችን መጠቀምና በየጊዜው መቀያየር ያስፈልጋል፤

• በይነ-መረብ ተጠቅመው ለተለያዩ አገልግሎት የሚያውሏቸውን ሶፍትዌሮችን ማዘመን፤

• የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምዎን ማስተካከል፡- የተለያዩ የግል መረጃዎችን በሚጠቀሟቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች ከመግለፅ መቆጠብ፤

• በተለያዩ የመረጃ ደህንነት ጉዳዮች ላይ ወቅቱን የጠበቀ የመረጃ አያያዝ እዉቀትን ማሳደግ፤

• በራስዎ ላይ የማንነት ስርቆት እንደተፈፀመ የሚያመላክቱ ነገሮች ካስተዋሉ በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ የይለፍ-ቃልዎን መቀየርና ለሚመለከታቸው ህጋዊ አካላት ሪፖርት ማድረግ፤

• የማንነት ስርቆት በማንኛውም ቦታ ሊፈፀም እንደሚችል ማወቅ፤ ለምሳሌ ጉዞ በሚያደርጉበት ጊዜ ወዴት እንደሚሄዱ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩና ሌሎችንም ተያያዥ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከማጋራት መቆጠብ እንደሚያስፈልግ ከኢመደአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡