አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በመካከለኛው አውሮፓ በሚገኙ ሀገራት በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መፈናቀላቸው ተገለፀ፡፡
ለቀናት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ኦስትሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ እና ሮማኒያ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ስሎቫኪያ እና ሀንጋሪም ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው ሀገራት መሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡
በአደጋው በሮማኒያ ስድስት፣ በኦስትሪያ አንድ እንዲሁም በፖላንድ አንድ በአጠቃላይ ስምንት ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ በአደጋው የከፋ ጉዳት ባስተናገደችው ቼክ ሪፐብሊክ አራት ሰዎች የገቡበት ያልታወቀ ሲሆን፤ 260 ሺህ ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል እንዳጡ እና ዲ1 የተሰኘው የፍጥነት መንገድ አግልግሎት ማቆሙ ተገልጿል፡፡
አደጋውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀባት ኦስትሪያ 1 ሺህ 100 ቤተሰቦች አካባቢያቸው ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል።
በፖላንድ 25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የክሎዦኮ ከተማ እና 75 ሺህ ነዋሪዎች ባሏት ጀለኒያ ጎራ ከተማ አደጋው መከሰቱን የሲጂቲኤን ዘገባ አመልክቷል።