የሀገር ውስጥ ዜና

ለክትመት እንቅፋት የሆነውን ኢ-መደበኛ አሰፋፈር ማስተካከል እንደሚገባ ተመላከተ

By Melaku Gedif

September 14, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የክትመት ምጣኔን ለማሳለጥ ኢ-መደበኛ አሰፋፈርን መልክ ማስያዝ እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ሄለን ደበበ እንደገለጹት÷ የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት ያሳካችውን ልምድ ያካፈለችበት ከሌሎችም ልምድ የቀሰመችበት ነበር።

በተለይም የኮሪደር ልማቱ በአዲስ አበባ ከተማ አጭር ጊዜ ውስጥ ያመጣው ለውጥ ትልቅ ልምድ የተቀሰመበት መሆኑን አንስተዋል።

በአፍሪካ ከተሜነት ገና ቢሆንም የክትመት ምጣኔው በፍጥነት እያደገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷በፍጥነት እየመጣ ያለውን ክትመት የሚመጥን የመሰረተ ልማት ግንባታ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ያለው የክትመት ምጣኔ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር እስከ 2050 የከተማ ነዋሪዎችን በእጥፍ ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለክትመት እንቅፋት የሆነውን ኢ-መደበኛ አሰፋፈር መልክ ማስያዝ እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም በትኩረት እየሰራች መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

በአፍሪካ ያለው የተፈጥሮ ኃብትና የሰው ኃይል አቅም ለከተሜነት መስፋፋት ገንቢ አበርክቶ እንዳለው ጠቁመው ÷በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ፈተና ይዞ እንደሚመጣም አስገንዝበዋል።