የሀገር ውስጥ ዜና

በቢሾፍቱ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የቱሪስት መስኅብነቷን ይጨምራል – ከንቲባ አዳነች

By ዮሐንስ ደርበው

September 13, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቢሾፍቱ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ሲጠናቀቅ የቱሪስት መስኅብነቷን በይበልጥ እንደሚጨምር የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት የሥራ መመሪያ መሠረት ከንቲባዋ በቢሾፍቱ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ከጉብኝታቸው ጎንለጎንም ከከተማዋ አመራሮች፣ ከነዋሪ ተወካዮች ፣ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተያዙ እቅዶች እና በቅንጅት በሚሰራበት ሁኔታ  ላይ መምከራቸውን ነው የገለጹት፡፡

የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ በአምስት አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ÷ ይህም የመንገድ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ እና መንገዶችን የማስዋብ ተግባራትን እንደሚያካትት አመላክተዋል፡፡

እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ሲጠናቀቅም በይበልጥ የቱሪስት መስኅብነቷን ይጨምራል፤ የከተማዋን የወደፊት ዕድልም ከፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡